የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች መልእክት
የዋና ዳይሬክተሯ መልዕክት
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች፣ የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አወጋገድ ረገድ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በመገንባት፣ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ በጥናት ላይ በመመርኮዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደርን ለማስፈን እየሰራ ይገኛል፡፡ባለስልጣኑ የህግ፣ የአሰራር እና የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ የሰው ሀይል አቅም በመገንባት እና አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ሥርዓትና ቁጥጥርን በማጠናከር የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም እንዲያስገኝ ለማስቻል እንዲሁም አፈጻጸሙ በአለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው መስፈርቶች ሲመዘን ውጤታማነቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን የባለስልጣኑን አገልግሎትና አስተዳደር የማሻሻያ ስራዎችንም እየሰራ ይገኛል፡፡በመሆኑም በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለማስወገድ በየበጀት ዓመቱ ለመንግስት ግዥ የሚመደበው ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ ተመጣጣኝ የሆነ ፋይዳ እንዲያስገኝ እና በከፍተኛ ወጪ የተገዛው ንብረት ከብክነት በጸዳ መንገድ ሥራ ላይ የሚውልበትን የአሰራር ሥርዓት በማጠናከር ለሀገራዊ ሁለተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡በመሆኑም ለዚህ እቅድ መሳካት ሥራዎችን ህግና አሠራርን መሠረት በማድረግ በቅንጅትና በትብብር መስራት ወሳኝ በመሆኑ ባለስልጣኑ የሚመለከታቸው የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት በተለይ የሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች አመራርና ፈጻሚዎች ዘርፉ በላቀ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቀባችሁን ሚና እንድትወጡ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ በባላስልጣኑ በኩል ለሰመረ የስራ ግንኙነትና ለውጤታማነት ያለሰለሰ ጥረት እንደሚደረግ ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር
የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት
የመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ተግባራት ከፌደራል መንግስት ዓመታዊ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወሰድ ጥናቶች የሚያመለክቱ ሲሆን ይህ ከፍተኛ የመንግስት ሃብት ቁጠባንና ቅልጥፍናን በተላበሰ መልኩ ያለብክነት ስራ ላይ እንዲውል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደርን በመርህ ማከናወን የግድ ነው፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዋነኛ መርህ ደግሞ በግዥ አፈጻጸም ረገድ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ተመጣጣኝ ፋይዳ ወይም ጥቅም ማስገኘት እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሰረት ባለስልጣኑ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ እንዲሁም ፍትሐዊ፣ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል በአማካሪ በተከናወነ ጥናት መነሻነት የግዥና ንብረት አስተዳደር ሥራዎች በዘርፉ በሰለጠኑ ሙያተኖች እንዲመራ የሚያስችል የኃላፊዎች እና ባለሙያዎችን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ በBasic, Essential እና Advanced ደረጃዎች የፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠና በመስጠት የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም የመገንባት ሥራዎችን እያከናወነ ያለ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዥ ፈጻሚ መ/ቤቶች የግዥ አፈጻጸማቸውን የሚመዝኑበት ቁልፍ የግዥ አፈጻጸም መለኪያዎችን በማዘጋጀትና ክትትል የማድረግ ሥራ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር የህግ ማዕቀፍ የማሻሻል፣ በግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ ረገድ ከግሉ ዘርፍ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የማጣራት እና ውሳኔ አሰጣጥን ግልጽ እና ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ፣ የግዥና ንብረት ኦዲትና ቁጥጥር ሥራዎችን የማጠናከር፣ ዘመናዊ እና በኤሌክትሮኒክ የተደገፈ የመንግስት ግዥ ሥርዓት እንዲኖር የማድረግ፣ የከፍተኛ የሃብት ብክነት የሚታይበትን የመንግስት ተሽከርካሪ አጠቃቀምና ቁጥጥርን ሊያግዝ የሚችል fleet Management System የማበልጸግ እና ሌሎች በርካታ የሪፎርም እና ማሻሻያ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡
ስለሆነም በዘርፉ ለሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት እነዚህን የሪፎርም እና ማሻሻያ ሥራዎችን በማጠናከርና፣ሥርዓቱን የበለጠ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም ዓቀፍ መመዘኛዎች አንጻር ተቀባይነት ያለውና ከበርካታ አገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የመንግስት ግዥና ንብረት አስዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ባለስልጣኑ የበለጠ ጠንክሮ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ ተገልጋዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተከናወነ ለሚገኘው የማሻሻያ ሥራ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡