የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በሀገራችን ከሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ከትግራይ ክልል ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዉጪ) ጉዳዩ የሚመለከታቸው የግዥ እና ንብረት አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴዎች የተሳተፉበት በዩኒቨርሲቲዎች አከባቢ የሚታዩ የግንባታ ግዥ፣የምክር አገልግሎት ግዥ፣ውል አስተዳደር እና በንብረት አስተዳደርና አወጋገድ ዙሪያ ከነሐሴ 4 እስከ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት በሶስት ክላስተሮች በመከፋፈል በአርባ-ምንጭ፣ በደብረ-ማርቆስ እና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
የአቅም ግንባታ ሥልጠው ዋና ዓላማ ግልፅ፣ ዘመናዊ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር ማስፈን፣ የመንግስትን ንብረት በጥንቃቄ የመያዝ፣ የመጠቀምና የመቆጣጠር እንዲሁም ንብረቱ አገልግሎቱ ሲያበቃ በወቅቱና በተገቢው መንገድ እንዲወገድ ማስቻል ነው፡፡
የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ትዉልድን በመቅረፅ ከሚያደርጉት ጎን ለጎን በግዥ አፈፃጸም ተግዳሮቶች፣ በልዩ ግዥ ፍላጎት መበራከት፣ በአቤቱታ እና ጥፋተኝነት ጉዳዮች መብዛት እና በግዥ አፈፃፀም ዙሪያ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶች፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች የጨረታ ሂደት ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎቻቸዉ እንዲሁም በአጠቃላይ በግዥ ዙሪያ የሚታዩ የግብዓት ጥራት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እና ሌሎች የአሰራር ግድፈቶችን በመቅረፍ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡
መንግስት ከመንገድ ግንባታ ቀጥሎ ከፍተኛ በጀት የሚመድብ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያንቀሳቅሱት በጀት ከፍተኛ በመሆኑ በየተቋማቶቹ የሚገኙ የግዥ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች በግዥ ዘርፍ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ማስገኘት የሚገባቸው መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች ስልጠናውን በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
በባለስልጣኑ በኩል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችም ሆነ ለባለሙያዎች ተደጋጋሚ በግዥና ንብረት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን የሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የባህሪይ ለውጥ በማምጣት በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች እየታየ ያለው የኦዲት ክፍተት በአግባቡ መታየትና መሻሻል ይገባዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሁሉም የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ብሎም ምርምር ለማካሄድ ግዥ የጀርባ አጥንት በመሆኑ፤ የሚገዙ ግዥዎችን በጊዜና በጥራት መግዛት እንደሚገባ እንዲሁም ህግና ስርዓትን የጠበቀ የግዥና የንብረት አስተዳደር ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡
በሶስቱም የክላስተር የተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ከ600 በላይ የግዥና ንብረት ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡